ትግራይና ኢትዮጵያ:ተጠይቆ ያልተሰማው የስርዓት ጥያቄና ሳይጠየቅ የተሰማው የመገንጠል ጥያቄ

ድምፂ ወያነ ታህሳስ 2/2011 (ተጠይቆ ያልተሰማው የስርዓት ጥያቄና ሳይጠየቅ የተሰማው የመገንጠል ጥያቄ )

አቶ ጌታቸው ረዳ የህወሀት/ኢህአዴግ ስራ-አስፈፃሚ አባል ናቸው፡፡ ከህወሀት ባለስልጣናት ቀለል ያለ አቀራረብ ያላቸው ናቸው፡፡ አቶ ጌታቸው ወደ ትግራይ ክልል የሚመጡ እንግዶችን ከተራ ዜጋ እስከ-ባለስልጣን ያለልዩነት ጠብ ርግፍ ብለው ያስተናግዳሉ፡፡

ይኼ ግላዊ ባህሪያው እንደተጠበቀ ሆኖ እንደመንግስት ክልላቸውን ወክለው በሚሰጡት አስተያየት የብዙሀኑን ቀልብ በመሳብ ደሞ ይታወቃሉ፡፡ ከሰሞኑ አስተያየት ከሰጡባቸው ጉዳዮች መካከል የመቐለው ሰልፍ አላማን በሚመለከት ነው፡፡ አቶ ጌታቸው በዛሚ ሬድዮ ክብ ጠረጴዛ ፕሮግራም ላይ በጋዜጠኞች ከተጠየቁት ጥያቄ መካከል " በመቐለው ሰለፍ ላይ የመገንጠል ጥያቄ ተንፀባርቋል ወይ?" የሚል ነበር፡፡ እኔም ለዛሬ የውይይት ርዕስ መነሻ ያደረኩት ይህንኑ ጥያቄ ነው፡፡ ለመሆኑ የትግራይ ህዝብ ከኢትዮጵያ የመገንጠል ፍላጎት አለው?

ኢትዮጵያ እና የትግራይ ህዝብ
-----------------------------
ለውይይታችን መነሻ የሚሆነው "የትግራይ ህዝብ ከኢትዮጵያ ለመገንጠል የሚያስችሉ ታሪካዊ መነሻዎች አሉ ወይ?" የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ የትግራይ ህዝብ ከኢትዮጵያ ጋር ያለው ትስስር ረጅም አመታቶችን ወደ ኋላ የሚጓዝ ነው፡፡ በዚህ የረጅም ጊዜያት ታሪካዊ ትስስር የትግራይ ህዝብ ከኢትዮጵያ ጋር በባህል በሀይማኖት በቋንቋ ወዘተ የተሳሰረ ነው፡፡ ትስስር ብቻም ሳይሆን ኢትዮጵያ ውስጥ ላሉት ከፍተኛ ትርጉም ያላቸው የታሪክ እና የባህል ፀጋዎች መነሻም ነው ትግራይ! ክርስትናና እስልምና ወደ ኢትዮጵያ የገቡት በአክሱም በኩል ነው፡፡ የአሁኗ ኢትዮጵያ ባህልና የሞራል ማንነት በእነዚህ ሀይማኖታዊ እምነቶች ላይ የተገነባ ነው፡፡ በዚህ መነሻነት የትግራይ ህዝብ ከሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር የሚጋራው ሞራላዊ መሰረት አለው፡፡

ከፖለቲካ አንፃር ካየነውም ስልጣን የመጋራት የእክልነትና መሰል ጥያቄ ካልሆነ የትግራይ ህዝብ ላይ የመገንጠል ጥያቄዎችን ሊፈጥሩ የሚያስችሉ ታሪካዊ መሰረቶች የሉም፡፡ ይሔን ለመረዳት ደግሞ ኢትዮጵያን ከውጪ ጠላቶች ለመጠበቅ ያደረጋቸው ታሪካዊ ተጋድሎዎችን ማስታወስ በቂ ነው፡፡ በአፄ ዮሀንስ ዘመን ከግብፅና ከሱዳን ድርቡሾች ጋር ያደረገው ተጋድሎ ፣ በአደዋ ጦርነት የነበረው የላቀ ተሳትፎ ፣ አለፍ ሲልም በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ላይ ያሳየው ኢትዮጵያዊ ትግል የመገንጠል ጥያቄው ታሪካዊ መሰረት አንደሌለው የሚያሳይ ነው፡፡

የትግራይ ህዝብ ለኢትዮጵያ ያደረጋቸውን እነዚህን ታሪካዊ ተጋድሎዎች በጥልቀት መመርመር ለቻለ ኢትዮጵያ እና የትግራይ ህዝብ በታሪካዊ ተጋድሎ የተገነባ ጠንካራ ትስስር አንዳላቸው መረዳት ይችላል፡፡

ህወሀትስ የመገንጠል ጥያቄ ይኖራት ይሆን?
------------------------------
ብዙ ሰዎች የትግራይ የመገንጠል ጥያቄ መነሻ አድርገው የሚወስዱት ህወሀትን ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ አንደመከራከሪያ የሚያነሱት አሳብ " ህወሀት መጀመሪያ ትጥቅ ትግል የጀመረችው የትግራይ ህዝብን ነፃ ለማውጣት ነው፡፡" የሚል ነው፡፡ እንደእነዚህ ሰዎች እምነት ህወሀት የትጥቅ ትግል ያደረገችው ትግራይ ለመገንጠል ነው፡፡ ከዚህ አለፍ ብለውም አንቀፅ 39 በህገ-መንግስቱ ላይ የተረቀቀው ይህንኑ አላማ ለማሳካት አንዲያመች ነው በሚል ይከራከራሉ፡፡ ስለዚህ እነዚህ ሰዎች በሌላ አነጋገር የትግራይ ህዝብ የመገንጠል ጥያቄ ከህዝቡ ካልተነሳ ከህወሀት ሊነሳ ይችላል እንደማለት ነው፡፡
" ህወሀት ትጥቅ ትግል የጀመረችው የትግራይ ህዝብን ነፃ ለማውጣት ነው፡፡" የሚለው መከራከሪያ አሳብ የሚነሳው የህወሀትን የትጥቅ ትግል ከሌሎች መሰል የትጥቅ ትግሎች ጋር ደባልቆ የመዘባረቅ ችግሮች ካሉባቸው ሰዎች መሆኑ የመጀመሪያው ጉዳይ ነው፡፡ በእርግጥ ለትግራይ ብሔራዊ ነፃነት ሲታገሉ የነበሩ ሃይሎች የሉም ማለት አይቻልም፡፡ ነገር ግን ይሄን አጀንዳ ሲያራምዱ የነበሩት ህወሀት የትጥቅ ትግሉን ከመቀላቀሏ በፊት የነበሩ የፖለቲካ ሃይሎች አንጂ ህወሀት አልነበረችም፡፡ ከዚህ አንፃር ይህን የተሳሳተ አጀንዳ ከብሔር መብት አንፃር በመቃኘት ያስተካከለችው ህወሀት መሆኗን ከታሪክ መማር የሚችል ሰው ካለ ህወሀት የመገንጠል ጥያቄ ምንጭ ልትሆን የምትችልበት ታሪካዊ መሰረት አንደሌለ መረዳት ይችላል፡፡

በሁለተኛ ደረጃ የመገንጠል ጥያቄ በህወሀት ውስጥ ተፈጥሮ ቢሆን አንኳ በጥቂት ሰዎች አንደ አማራጭ ቀርቦ በአስተሳሰብ ትግል የከሰመ አንጂ የህወሀት ገዝ አጀንዳ ሆኖ አለመምጣጡንም መረዳት ተገቢ ነው፡፡ ምክንያቱም ትግራይ ውስጥ እንደ አንድ ፖለቲካዊ ሀይል ለመቆየት የግድ የትግራይን ከላይ የተገለፀው መሰረታዊ ባህሪ ጠንቅቆ ማወቅ እና መከተል የግድ ይላል! በመሆኑም ባለፉት 27 ዓመታትም ቢሆን ከታሪካዊ መነሻም ይሁን ከፖለቲካዊ መነሻ ህወሀት ኢትዮጵያ ውስጥ ጠንካራ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት አንዲገነባ ከመታገል ውጪ የመገንጠል ጥያቄን የምታራግብበት ፓርቲ ሆና አትታየኝም፡፡ አሁንም የምታደርገው ትግል ኢትዮጵያ ያላት የስርዓት መሰረት ተንዶ አገራዊ ህልውናዋ አደጋ ላይ አንዳይወድቅ ከመታገል ውጪ ሌላ አጀንዳ ለማራመድ መዋቅራዊ ባህሪዋ የማይፈቅድላት መሆኑን ከግንዛቤ ቢወሰድ መልካም ነው፡፡

የመገፋት ስሜት
-------------------
እና ጥያቄው ከየት መጣ? አቶ ጌታቸው እንደተናገሩት በትግራይ ህዝብ ዘንድ የመገፋት ስሜት አንጂ የመገንጠል ጥያቄ የለም፡፡ የመደመር ፖለቲካ ከተጀመረ በኋላ የትግራይ ህዝብ ላይ ያነጣጠሩ አካላዊና የስነ-ልቦና ጥቃቶች ተስፋፍተዋል፡፡ እነዚህ ደግሞ በትግራይ ህዝብ ዘንድ የመገፋት ስሜትን መፍጠራቸው የማይቀር ነው፡፡ በዚህ መሀል ይኼን የመገፋት ስሜት በመጠምዘዝ በተዛባ መንገድ የመገንጠል ጥያቄ አድርገው የሚወስዱ አጀንዳ ጠምዛዦች ተፈጥረዋል፡፡

እንደ አቶ ጌታቸው እምነት ይህንን ችግር የሚፈጥሩ ደንቆሮዎች ከትግራይ ህዝብ ውስጥ ብቻ ሳይሆን ከየትኛው አቅጣጫ ሊፈጠሩ ይችላሉ፡፡ ግራም-ነፈሰ ቀኝ አቶ ጌታቸው የህዝባቸውንም የፓርቲያቸውንም አቋም በግልፅ አንዳስቀመጡት የትግራይ ህዝብም ይሁን ህወሀት የመገንጠል ጥያቄ እንዳላቀረቡ ነው፡፡ ከመገንጠል ጥያቄው ይልቅ በተግራይ ህዝብ ዘንድ በተደጋጋሚ ሲቀርቡ የነበሩት የኢትዮጵያን አንድነት የሚያጠነክሩ እና አገርን ከመፍረስ አደጋ የሚያድኑ የህግ የበላይነትን የሚጠይቁ "የመርህ ይከበር!" ጥያቄዎች ናቸው፡፡

የመልስ ምት
-----------------
አቶ ጌታቸው በጉዳዩ ላይ የሰጡት ምላሽ ከውጭም ከውስጥም ለሚነሱ አጀንዳ አራጋቢዎች የሚሆን ጠንካራ የመልስ ምት ነው፡፡

በአንድ በኩል ከውስጥ ያሉ ኃይሎች የትግራይ ህዝብ የፈጠረውን የመገፋት ስሜት በመጠምዘዝ የመገንጠል ጥያቄ በማራገብ የመንጋ ፖለቲካ ለመፍጠር ለሚንቀሳቀሱ ኃይሎች የተሰጠ የመልስ ምት ነው፡፡ በሌላ በኩል ከክልሉ ፖለቲካ ውጪ የሚንቀሳቀሱ ሃይሎች የትግራይ ህዝብ የጠየቀውን የስርዓት ይከበር ጥያቄ መመለስ ሲያቅታቸው ባልተጠየቀ የመገንጠል ጥያቄ የህግ የበላይነትን ለማዳፈን ለሚፈልጉ ኃይሎች ማስተማሪያ ነው፡፡ ከዚህ በተረፈ የትግራይ ህዝብ የጠየቀው የስርዓት ጥያቄ ሳይሰማ ያልጠየቀው የመገንጠል ጥያቄ መደመጡ ለብዙዎች የሚያስተዛዝብ ነው፡፡

በመጨረሻ አቶ ጌታቸው ባስቀመጡት አሳብ አሳቤን መቋጨት እፈልጋለሁ፡፡ እንደ ትግራይ ህዝብ "ትናንትም ኢትዮጵያዊ ሆነን ኖረናል፡፡ ነገም ኢትዮጵያዊ ሆነን አንኖራለን"

ቸር እንሰንብት!

/ዘመንፈስ አክሱማዊ/