የህወሀት የትግል ታሪክ

መቐለ 13 ለካቲት 2011(ድምፂ ወያነ) (ህወሀትን ትግል ልዩ የሚያደርገው ምንድን ነው?)

በኢትዮጵያ ፖለቲካ ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት የታገለችው ህወሀት ብቻ አልነበረችም፡፡

ከንጉሱ ጀምሮ እስከ ደርግ ስርዓት ለዴሞክራሲ የታገሉ የፖለቲካ ኃይሎች በርካታ ነበሩ፡፡ ይሁንና የህወሀት ትግል የሚፈለገውን ውጤት በማምጣት በኩል የተለዬ ነበር፡፡

ህወሀትን ከሌሎች የፖለቲካ ኃይሎች የተለዬ ያደረጋት ደግሞ ካላት ታሪካዊ የአልበገሬነት መንፈስ በተጨማሪ ትከተለው የነበረው የትግል ስልት ነው፡፡ ይህ የልዩነት መነሻ ምንድን ነው?

የህወሀትን ትግል በውጤታማነቱ የተለዬ የሚያደርጉ ጉዳዮች ሁለት አይነት መነሻዎች ያሏቸው ናቸው፡፡ የመጀመሪያው የነበራቸው ጠንካራ ህዝባዊ መሰረት ነው፡፡ ሁለተኛው የፖለቲካ መስመራቸው ጥንካሬ ነው፡፡

በመጀመሪያ ከህዝባዊ መሰረት አንፃር ካየነው ህወሀትን የፈጠራት የትግራይ ህዝብ ነው፡፡ ከህወሀት ውጪ የነበሩ የፖለቲካ ትግሎች የከሸፉበት ምክንያት አንድም ህዝባዊ መሰረት መፍጠር ባለመቻላቸው ሁለትም መሰረት ያደረጉበት ማህበረሰብ ለአብዮታዊ ትግል የሚሆን ምቹ መሰረት ስሌለው ነው፡፡ ለአብነት ያህል የ60ዎቹ ወጣቶች ንቅናቄ ወቅቱ የፈጠረው የማርክስ ሌኒነዝም አብዮት ፋሽን የፈጠራቸው ቀለም-ቀመስ ሊሂቃን ናቸው፡፡ ይህ የሊሂቃን ንቅናቄ ህዝባዊ መሰረት የሌለው ቢኖረውም ለአብዮታዊ ትግል ምቹ መሰረት የሌለው በመሆኑ ደርግን ተክቶ ከማለፍ ውጪ አላማውን ማሳካት አልቻለም፡፡ በተመሳሳይ የከተማ ላይ አመፅ ከተወሰነ የትጥቅ ትግል ጋር እያጠቀሰ ሲንቀሳቀስ የነበረው ኢህፓ ከውድቀቱ ጀርባ ህዝባዊ መሰረት መፍጠር አለመቻሉ ዋናው ምክንያት ነው፡፡ እንደ መኢሶን አይነቶቹ ህዝብን ትተው ደርግን ራሱን የትግላቸው መሰረት በማድረጋቸው በራሱ በደርግ ተበልተው ጠፍተዋል፡፡

በአንፃሩ ህወሀት እንደሌሎቹ ወቅቱ የማርከስ-ሌኒንስት አብዮት ፋሽን የፈጠራት ሳትሆን ከህዝብ ጥያቄ በመነሳት የተፈጠረች ፓርቲ ናት፡፡ በዚህም ሰፊ የሆነ ህዝባዊ መሰረት ላይ ትኩረት በመስጠት በትግሉ ሂደት ጠንካራ የህዝብ ተሳትፎ አንዲፈጠር አድርጋለች፡፡ በትግሉ ወቅት የትግራይን የህዝብ ሞራልና የፖለቲካ ተሞክሮ ውጤታማ በመሆነ መልኩ መጠቀም መቻሏም በትግሏ ስኬታማ አንድትሆን አስችሏታል፡፡ ገዥ የሆነ ፖለቲካ አስተሳሰብ በመፍጠር ሰፊ ህዝባዊ መሰረት የነበራት ህወሀት ከዚህ አንፃር ብቃት ያለው የህዝብ ተወካይ በመሆን መታጋሏ ከሌሎች የትግል ኃይሎች ውጤታማ ትግል እንድታደርግ በማገዝ በኩል የጎላ አስተዋፅኦ አለው፡፡

በሌላ በኩል ህወሀት የጠራ የፖለቲካ መስመር መፍጠር መቻሏም የልዩነቱ መነሻ ነው፡፡ የትግል ስትራቴጂ በአካላዊ ትግል ቆረጣን የመሳሰሉ ወታደራዊ ስትራቴጂዎች በአስተሳሰብ ትግሉ የግምገማ ባህል መኖሩ ህወሀትን በትግል ውጤታማ ያደረገ የፖለቲካ መስመር ነው፡፡ ብዙዎቹ በዴሞክራሲ ስም በሚምሉበት በያኔው የአብዮት ፋሽን ወቅት ከህወሀት ውጪ ያሉት ትግሎች የአጀንዳ ጥራት ችግር የነበረባቸው ናቸው፡፡ መኢሶን የደርግ ተለጣፊ አንደመሆኑ መጠን አላማው ደርግን ማስተካከል እንጂ ዴሞክራሲያዊ አጀንዳን ማሳካት አልነበረም፡፡ ኢህአፓም ቢሆን አብዛኛውን አርሶ አደር በሚመለከት የነበረው የመሬት ሀብት አጠቃቀም በሚመለከት የተምታታ አቋም ነበረው፡፡ አንደ ኢዲዩ አይነቶቹ ደርግ ላሽቀነጠራቸው ፊውዳሎች ማንሰራራት የሚታገሉ ስለነበሩ አልተሳካላቸውም፡፡

በአንፃሩ ህወሀት ከዴሞክራሲ አንፃር የብሔር-ብሔረሰቦች እኩልነት እና የራስን መበት በራስ የመወሰን አጀንዳን ጥርት ባለ-መልኩ በማስቀመጥ ለዚሁ የፖለቲካ መስመር መታገሏ የህዝብ ውግንና አንዳላት ያስመሰከረ ነው፡፡ ውጤታማ ያደረጋትም ይኸው ህዝብን ያማለከ ውጤታማ የፖለቲካ መስመር መከተሏ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ህዝባዊ መሰረት ያለው በጠራ የፖለቲካ መስመር የተመራ አብዮታዊ ትግል ማሳካት የቻሉት የትግራይ ህዝብና ህወሀት ናቸው ቢባል ማጋነን አይሆንም ማለት ነው፡፡

መልካም የምስረታ በዓል!

ዘመንፈስ አክሱማዊ
ድምጺ ወያነ፡ የካቲት 12/2011