የቀለም አብዮት በኢትዮጵያ!

ድምፂ ወያነ፡ መጋቢት 6/2011 1. የቀለም አብዮት በኢትዮጵያ በ1960ዎቹ የተጨናገፉ የፖለቲካ ትግሎች ዛሬ እየሰሩ ይመስላል፡፡ አንደኛው መንጋ ላይ ጥገኛ ያደረገ የፖለቲካ ትግል ነው፡፡ ሁለተኛው መንግስት መዋቅሩን ጥገኛ ያደረገው የፖለቲካ ትግል ነው፡፡ ከ60ዎቹ አንስቶ እስከ ደረግ ዘመን የቀለም አብዮት ሊሳካ የሚችልበት አድል አልነበረውም፡፡ ፡፡ ምክንያቱም ደግሞ ጥገኛ የሆነበት የፖለቲካ መሰረት ምቹ ባለመሆኑ ነው፡፡ በወቅቱ ስርዓቶቹ ካላቸው አምባገነናዊ ባህሪ የተነሳ ለጥገኛ ትግል ምቹ አልነበሩም፡፡ ከዚህ አንፃር ደርግ በነበረው አንባገነናዊ ባህሪ የተነሳ መኢሶንና ኢህአፓን በቀላሉ ማጥፋት ችሎ ነበር፡፡ በንጉሱ ወቅት መንጋን ጥገኛ ማድረግ የሚያስችል የቀለም አብዮት መሰረት ባለመኖሩ ንጉሱ እስከ እርጅና ዘመናቸው ድረስ ገዝተዋል፡፡ ንጉሱ ሲያረጁ ስርዓታቸውም አብሯቸው አረጀና የወጣቶቹ ንቅናቄ አስወገዳቸው፡፡ ነገር ግን ይ የቀለም አብዮት አልነበረም፡፡ ንጉሱ የወረዱት እሳቸውም ስርዓታቸውም አርጅቶ እንጂ በቀለም አብዮት አልነበረም፡፡

አቶ መለስ ይመሩት በነበረው የኢህአዴግ መንግስትም ጠንካራ መዋቅር ተፈጥሮ ስለነበር የቀለም አብዮት አልተሳካም፡፡ ከእሳቸው በኋላ ግን የቀለም አብዮት አቁጥቁጦ ጥርስ አበቀለ፡፡ ኢህአዴግ በአመራር ችግር ህዝባዊ ክንፉንም የራሱንም መዋቅር መቆጣጠር ሲያቅተው የቀለም አብዮት ጥገኛ መሆን የሚችልበት ምቹ ሁኔታን ተፈጠረ፡፡ ከዚህ አንፃር አንድም መዋቀሩን ጥገኛ ባደረጉ ሁለትም መንጋው ላይ ጥገኛ በሆኑ ኃይሎች ላይ የበቀለው የቀለም አብዮት ተሳክቶለት በኢትዮጵያ የፖለቲካ ለውጥ መፍጠር ቻለ፡፡

2. የቀለም አብዮት በአሁኑ ሰዐት
-------------------
አሁን ላይ የቀለም አብዮት በአገሪቱ ተሳክቷል፡፡
ለመሆኑ የቀለም አብዮት ምንድን ነው? የቀለም አብዮት ጥገኛ የፖለቲካ ትግል ነው፡፡

በአላማ ደረጃ የቀለም አብዮት የፖለቲካ አላማ የለውም፡፡ የቀለም አብዮት አለማ የስርዓት ለውጥ ሳይሆን ስርዓት ማፍረስ ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ የመንግስት ለውጥም አላማ የለውም፡፡ ከመንግስት አንፃር ዋንኛ አላማው መንግስትን ማዳካም ነው፡፡ የፖለቲካ አላማ ከሌለው ደግሞ የቀለም አብዮትን በአላማው ልንረዳው አንችልም፡፡ ስለዚህ ዋናው ባህሪው የትግል ስልቱ ላይ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር የቀለም አብዮት ከሁለት ዋሻዎች የሚነሳ ጥገኛ ትግል ነው፡፡

አንደኛው የጥገኝነት ዋሻው የመንግስት መዋቅር ነው፡፡ የመንግስት መዋቅሩ ከውስጥ በኩል ሲበሰብስ ለቀለም አብዮት ምቹ የሆነ ጥገኛ ዋሻ ይፈጥራል፡፡

ሁለተኛው የቀለም አብዮት የጥገኝነት ዋሻው ህዝባዊ መሰረት ነው፡፡ ህዝብ የምንለው ገዥ የሆነውን የፖለቲካ አመለካከት ነው፡፡ ይህ ገዥ አመለካከት ሲዳከም ለቀለም አብዮት ምቹ የሆነ የመንጋ አቅም ይፈጥራል፡፡

ለምሳሌ በኢትዮጵያ የተሳካው የቀለም አብዮት የተነሳው ሁለቱንም ዋሻዎች መነሻ አድርጎ ነው፡፡ በኢትዮጵያ የተሳካው የቀለም አብዮት በአንድ በኩል መንግስቱን ከሚመራው ከኢህአዴግ ውስጥ ነው፡፡ ኢህአዴግ የነበረው መዋራዊ ጥንካሬ እየተዳከመ ሲመጣ የመንጋ ፖለቲከኞች መፈልፈያ መሆን ጀመረ፡፡ የድርጅቱ አስተሳሰብና የተግባር አንድነት ተናግቶ ከውስጥ በኩል ሌላ ጥገኛ ኢህአዴግ ተፈጠረ፡፡ በሌለ በኩል በዚህ መልኩ ገዥ አስተሳሰቡ እየተሸረሸረ ሲሄድ በውጪ በኩል የቀለም አብዮትን ማሳካት የሚችል የመንጋ አቅም ተፈጥሮ የቀለም አብዮቱ ተሳካ ማለት ነው፡፡
3. የቀለም አብዮት እና የትግራይ ክልል
----------------------
በኢትዮጵያ የቀለም አብዮት በሚገባ ተሳክቷል ብለናል፡፡ በአብዛኛው አገሪቱ ክፍሎች በሚባል ደረጃ ስርዓት ፈርሷል፡፡ ወላፈኑ ያልነካው የትግራይ ክልል ነው፡፡ ከዚህ አንፃር በትግራይ ክልል ባለው ጠንካራ የመንግስት ስርዓት ትግራይን ክልልም እንደ ትንሽ ስርዓት መውሰድ አንችላለን፡፡ አሁን ጥያቄው አንድ ነው፡፡ የቀለም አብዮት በትግራይ ክልል ምልክቱ አለ ወይ?

በትግራይ የቀለም አብዮት ምልክት መኖራቸውን የህወሀት መዕከላዊ ኮሚቴ መግለጫ በማየት መገንዘብ ይቻላል፡፡ የኮሚቴው መግለጫ ክልሉ የሰላም አደጋ ተጋርጦበት የነበረ መሆኑን አልደበቀም፡፡ የትግራይ ህዝብንና መሪውን ድርጅት ህወሓትን ለማንበርከክ ከሁሉም አቅጣጫዎች ከፍተኛ ሴራዎች መኖራቸውን ጠቅሷል፡፡ መገለጫው ሳይንሳዊ የፖለቲካ ትግልን ከጠንካራ ህዝባዊ መሰርት ጋር በማቀናጀት የክልሉን የሰላም አደጋዎች በብቃት መቀልበስ መቻሉን ገልፀዋል፡፡ ይህ አሳብ የቀለም አብዮት ምልክቶች መኖራቸውን ጠቋሚ ነው፡፡

መግለጫው ሲቀጥል ለቀለም አብዮቱ ምልክቶች ያላቸውን ባህሪ የሚገልፅ አሳብ አስፍሯል፡፡ "... የህዝቡን ልማት ፣ጥያቄና ትግል ሌላ ትርጉም በማስያዝ ለዘመናት የዘለቀውና በአሁኑ ወቅት ተጠናክሮ የቀጠለውን አንድነት እድል አገኘን ብለው ለማደፍረስ ጥረት እያደረጉ ነው፡፡" ይህ አሳብ የምልክቱን ባህሪ በሚመለከት ፍንጭ ሊሰጠን ይችላል፡፡ ትክክለኛውን የህዝብ አጀንዳ ወደ ጥገኛ የፖለቲካ አጀንዳ በመጠምዝ የህዝቡን አንድነት በማናጋት ሰላም ማደፍረስ የሚፍለጉ እና ሰላም የሚያደፍርሱ ወዘተ የሚሉት አገላለፆች የቀለም አብዮቱ ምልክቶች አድረግን መውሰድ አንችላለን፡፡

ከዚህ በተጨማሪ መግለጫው የሚለው አለው፡፡ ህወሀትንና የትግራይን ህዝብ ፊት ለፊት ገጥመው ማንበርከክ ያልቻሉ ኃይሎች ሌላ የትግል አማራጭ መከተል መጀመራቸውን በመጥቀስ ህዝቡ ራሱ እንዲታገላቸው ጥሪ አቅርቧል፡፡ እዚህ ላይ "ሌላ የትግል አማራጭ" የሚለው የቀለም አብዮት ሊሆን አንደሚችል ግልፅ ነው፡፡ በዚህ መልኩ መግለጫው ምልክቱን ሲያጠናክር ባንዳ ተላላኪ ወዘተ በሚል ገልፅዋቸው አልፏል፡፡ ይህ ማለት ጥገኛ ትግል ላይ የተመሰረተ የቀለም አብዮት በትግራይ ምልክቱ እየታዬ ነው ማለት ነው፡፡ በመጨረሻ አንድ ጥያቄ ይቀረናል፡፡

4. የቀለም አብዮት በትግራይ ሊሳካ ይችላል?
---------------------
የቀለም አብዮት በትግራይ ሊሳካ የሚቻልበት እድል ወደ ማይቻል ደረጃ የወረደ ነው፡፡ ምክንያቱም የቀለም አብዮት ማሳካት የሚያስችል የፖለቲካና ማህበራዊ መሰረት በትግራይ የለም፡፡ የቀለም አብዮት ምን ይፈልጋል? የቀለም አብዮት እንዲሳካ በዋንኛነት ሁለት ጉዳዮች መሟላት አለባቸው፡፡ አንደኛው መዋቅራዊ መሰረት ነው፡፡

ሁለተኛው ህዝባዊ መሰረት ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ካየነው የቀለም አብዮት በትግራይ ሊሳካ የሚችልበት እድሉ በጣም ጠባብ ነው፡፡ ምክንያቱም ከመዋቅራዊ መሰረት አንፃር ክልሉን የሚመራው የህወሀት ፓርቲ መዋቅራዊ ባህሪው አልተዳከመም፡፡ አመራሩ ውስጣዊ ውህደትም ጤናማ ሊባል የሚችል ነው፡፡ ከዚህ አልፎ ከምንጊዜውም በላይ ህዝባዊ ተቀባይነቱ እየጨመረ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ለቀለም አብዮት ምቹ አድል የሚፈጥር መዋቅራዊ መሰረት የለም፡፡
ሁለተኛ በትግራይ ክልል የቀለም አብዮትን ሊያሳካ የሚችል የማህበራዊ መሰረት የለም፡፡

በክልሉ ያለው ጠንካራ ህዝባዊ መሰረት የመንጋ ፖለቲካን የሚያስተናገድ አይደለም፡፡ (በሌላ አነጋገር ህዝቡ ወደ መንጋነት አልተለወጠም፡፡ ወደ መንጋ ያልተለወጠ ማህበረሰብ ውስጥ ደግሞ የቀለም አብዮትን ማሳከት የሚቻልበት ሁኔታ ወደ ዜሮ የሚጠጋ ነው፡፡ ይህ በራሱ የገነባው ማህበረሰባዊ ብቃት እንደተጠበቀ ሆኖ የቀለም አብዮት በተሳካባቸው አካባቢዎች ጠንካራ መንግስት አልመሰረቱም፡፡ ስርዓት እየፈረሰ ነው፡፡ የፖለቲካ ለውጥ ወደ ነውጥ እየተቀየረ ዜጎች ለስደትና ለእንግልት እየተዳረጉ መሆኑን ህዝቡ እየታዘበ ነው፡፡ ስለዚህ በትግራይ ክልል የቀለም አብዮትን ሊያሳካ የሚችል ህዝባዊ መሰረት ሊኖር አይችልም፡፡
ከዚህ ውጪ በአሁኑ ወቅት ህዝቡ ለመሪ ድርጅቱ ህወሓት ከፍተኛ ድጋፍ እየሰጠ ይገኛል፡፡ በዚህ የተነሳ የቀለም አብዮት መሪዎች ህዝባዊ ድጋፍ አይኖራቸውም፡፡ እንዲህ ከሆነ ደግሞ የቀለም አብዮት መሪዎቹን በቀላሉ መቆጣጠር ይቻላል፡፡ በእነዚህና መሰል ምክንያቶች የተነሳ በትግራይ ክልል የቀለም አብዮት ሊሳካ የሚችልበት አድል ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ዝግ ነው፡፡ ስለዚህ የቀለም አብዮትን በትግራይ በተግባር ማሳካት አይቻልም ብቻ ሳይሆን ማሰብም በራሱ የማይታሰብ ነው፡፡