የሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ሚኒስቴር ከምዕራብ ጉጂ ዞን ለተፈናቃሉ ዜጎች የተለያዩ ድጋፎችን አደረገ

05 ግንቦት 2011(ድወት) ሚ/ር መ/ቤቱ ከተለያዩ አጋር አካላት በጋራ በመሆን ያሰባሰባቸውን የመጠለያ ድንኳን፣ የተለያዩ አልባሳትና የምግብ እህል በአጠቃላይ ከ1.5 (አንድ ነጥብ አምስት ሚሊየን ብር) በላይ የሚገመት ድጋፍ ማድረጉን አስታውቋል፡፡

ሚ/ር መ/ቤቱ ከ1 ወር በፊት ወደ ቦታዉ ተንቀሳቅሶ የተለያዩ ድጋፎችን ሲያደርግ ሴቶችና ህጻናትን ያሉበት ሁኔታ አስቸጋሪና ከፊትለፊት ያለዉ የዝናብ ሁኔታ ከባድ መሆኑን የተመለከተና በስፈራዉ የሚገኙ የሚ/ር መ/ቤቱ ባለሙያዎችም እጥረቱን በጊዜዉ በሚደረጉ የመረጃ ልዉዉጦች ይገልጹ ስለነበር ተጨማሪ ድጋፍ በመጠለያ ድንኳን ላይ በማተኮር የማሰባሰብ ስራ መሰራቱን ከማንጅመንት አባለቱ ጋር በቦታው ተገኝተው አስተያየት የሰጡት የሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ወ/ሮ ሕይወት ኃይሉ ሲሆኑ አክለዉም በስፍራዉ ሲደረስ ያለዉ ነባራዊ ሁኔታ ተፈናቃዮችን ወደ መኖሪያ ቄያቸዉ የማሰመለሱ ስራ ተጠናከሮ እየተሰራ እንዳለና ሌሎች በተጓዳኝ የሚሰሩ ስራዎችም እየተሰሩ እንዳሉ መገንዘባቸዉን አብራርተዋል፡፡

ተቋሙ በቀጣይም ተፈናቃዮቹ ወደ የቄያቸው ተመልሰዉ ሲጠናቀቅም በቀጣይ የሚያስፈልጉ ድጋፎችን ከሚመለከታቸዉ አካላት ጋር በጋራ በመሆን ከጎናቸዉ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

የጌዴኦ ዞን ምክትል ዋና አስተዳዳሪ አቶ ገዙ አሰፋ በበኩላቸው መንግስት እንደ መንግስት ምግብ ነክና ምግብ ነክ ያልሁኑ ቁሳቁሶችን ድጋፍ የማድረግ ስራ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው በቀጣይ እንዚህን ዜጎች በድጋፍ ማቆየት ስለማይቻል ወደ ቄያቸው የማሰመለስ ስራ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

አክለውም መልሶ የማቋቋምና የህግ የበላይነትን የማስከበር ስራውን የፌዴራል መንግስት ከክልሉ መንግስት ጋር በመቀናጀት ከመቸውም ጊዜ በተሸለ ሁኔታ በመስራት ችግሮቻቸውን ለመፍታት ከፍተኛ ጥረት እያደረገ መሆኑን ጠቅሰው

ዜጎች ወደ ቄያቸው እየተመለሱ ያሉበት ወቅት በመሆኑ አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ የቀድሞ ኑሯቸውን መኖር እንዲችሉ ከእርሻ መሳሪያ ጀምሮ አስፈላጊዉን ድጋፍ ለማመቻቸት እየተንቀሳቀሱ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ወደ ቄያቸዉ በመመለስ ላይ የሚገኙ ተፈናቃዮች በበኩላቸው መንግስት እያደረገላቸው ያለውን ድጋፍ አመስግነው ነገር ግን ከተደረገላቸው ድጋፍ በተጨማሪ ወደ ቄያችን በመመለስ ለመስራትና ወደ ቀድሞ ህይወታችን ለመመለስ፤ የእርሻ መሳሪያዎችንና ሌሎች ቁሳቁሶችን በመስጠት እንዲሁም ደህንነታችንን በማስጠበቅ መንግስት በሰላም ጉዳይ አጥብቆ እንዲሰራና ከጎናችን እንዲቆም ሲሉ ጠይቀወል፡፡

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ሚኒስቴር የላከልን መረጃ